1 John 5

በእግዚአብሔር ልጅ ማመን

1ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ የሚያምን ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልዷል፤ አባትንም የሚወድድ ሁሉ ልጁንም እንደዚሁ ይወድዳል። 2እግዚአብሔርን ስንወድድና ትእዛዞቹን ስንፈጽም የእግዚአብሔርን ልጆች እንደምንወድድ በዚህ እናውቃለን፤ 3እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዞቹን መፈጸም ነውና። ትእዛዞቹም ከባድ አይደሉም፤ 4ምክንያቱም ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋል። ዓለምን የሚያሸንፈውም እምነታችን ነው። 5ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ከሚያምን በስተቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማነው?

6በውሃና በደም የመጣው ይህ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ በውሃና በደም እንጂ በውሃ ብቻ አልመጣም። የሚመሰክረውም መንፈስ ነው፤ መንፈስ እውነት ነውና። 7ስለዚህ ሦስት ምስክሮች አሉት፤ 8እነርሱም
ጥንታዊ ባልሆነው በቩልጌት ቅጅ ላይ በሰማይ የሚመሰክሩት ሦስቱ ናቸው፤ እነርሱም አባት፣ ቃልና መንፈስ ቅዱስ ናቸው ይላል። 8 በምድር የሚመሰክሩት ሦስቱ ናቸው – ሆኖም ይህ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን በፊት በነበሩት የግሪክ ቅጆች ውስጥ አይገኝም።
መንፈሱ፣ ውሃውና ደሙ ናቸው፤ ሦስቱም ይስማማሉ።
9የሰውን ምስክርነት ከተቀበልን፣ የእግዚአብሔር ምስክርነት ከዚያም ይልቃል፤ ይህ ስለ ልጁ የሰጠው የእግዚአብሔር ምስክርነት ነውና። 10በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን ሁሉ በልቡ ምስክር አለው፤ ማንም እግዚአብሔርን የማያምን ሁሉ እግዚአብሔር ስለ ልጁ የሰጠውን ምስክርነት ስላላመነ ሐሰተኛ አድርጎታል። 11ምስክርነቱም ይህ ነው፤ እግዚአብሔር የዘላለምን ሕይወት ሰጠን፤ ይህም ሕይወት ያለው በልጁ ነው። 12ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም።

ማጠቃለያ ሐሳብ

13በእግዚአብሔር ልጅ ስም የምታምኑ እናንተ፣ የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ ይህን እጽፍላችኋለሁ፤ 14በእግዚአብሔር ፊት ለመቅረብ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ ማንኛውንም ነገር እንደ ፈቃዱ ብንለምን እርሱ ይሰማናል። 15የምንለምነውን ሁሉ እንደሚሰማን ካወቅን፣ የለመንነውንም ነገር እንደ ተቀበልን እናውቃለን።

16ማንም ሰው ወንድሙ ለሞት የማያበቃ ኀጢአት ሲያደርግ ቢያየው ይጸልይ፤ እግዚአብሔርም ለሞት የማያበቃ ኀጢአት ላደረጉት ሕይወትን ይሰጣል። ለሞት የሚያበቃም ኀጢአት አለ፤ ስለዚህኛው ግን ይጸልይ አልልም። 17ዐመፅ ሁሉ ኀጢአት ነው፤ ለሞት የማያበቃም ኀጢአት አለ። 18ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኀጢአት እንደማያደርግ፣ ነገር ግን የእግዚአብሔር ልጅ እንደሚጠብቀው፣ ክፉውም እንደማይነካው እናውቃለን። 19እኛ ከእግዚአብሔር እንደ ሆንን፣ መላው ዓለምም በክፉው ሥር እንደ ሆነ እናውቃለን።

20የእግዚአብሔር ልጅ እንደ መጣ፣ እውነተኛ የሆነውን እርሱን እንድናውቅ ማስተዋልን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እኛም እውነተኛ በሆነው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አለን። እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው።

21ልጆች ሆይ፤ ራሳችሁን ከጣዖቶች ጠብቁ።

Copyright information for AmhNASV